በሐዋሳ ከተማ ከትላንት ጀምሮ የብልጽግና ካድሬዎች ነጋዴውን በማስገደድ ብሩን እየነጠቁት ነው ሲሉ ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 ገለጹ።
በተደጋጋሚ ቀን እየተቆጠረ እንዲህ አይነት አይን ያወጣ ሌብነት ሲፈጸም ቢቆይም ትላንት የጀመረው የብር አምጡ ዘመቻ ግን ሃይል የተቀላቀለበት ነው ብለዋል።
ለብር ጥየቃው ምክንያት ተደርጎ የተቀመጠው ለብልጽግና ፓርቲ ገቢ ማሰባሰቢያ የሚል መሆኑን ነው ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ ያመለከቱት።
በጣም በአነስተኛ የንግድ ስራ ላይ የተሰማራ ነጋዴ በትንሹ የሚጠየቀው ከ2ሺ ብር በላይ የሆነ ገንዘብ ነው ይላሉ።ሌላው ደግሞ ከዛ በላይ ሲሉ ይገልጹታል።
ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ የቀጠለው የብር ዝርፊያ ዘመቻው የንግዱ ማህብረሰብ አባላትን አስቆጥቷል ብለዋል።
የንግዱ ማህበረሰብም ሆነ ሌላው ህዝብ መኖር አቅቶት በፈተና ውስጥ ባለበት በዚህ ሰአት አይን ባወጣ መልኩ የሚካሄደው ሌብነት ከላይ ካለው አመራር የሚጀመርና ትእዛዙም ከዛ የሚወርድ መሆኑን ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ በመረጃቸው ላይ እንደሚሉት ከሆነ ብልጽግና የሚባለው ስብስብ ዋና የሚፈልገው ገንዘብ ሳይሆን አብዮት ቀስቅሶ የሚያስወግደውን አካል ብቻ ነው ሲሉ በምሬት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።