(ኢትዮ 360 -ሚያዚያ 25/2015) ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሰራዊት ያስጠጋው ህወሃት ንጹሃንን ለመፍጀት ዝግጅቱን አጠናቋል ሲሉ የኢትዮ 360 ምንጮች ገልጸዋል።
በማይፀብሪም በተመሳሳይ መልኩ ሃይሉን አስገብቷል የሚሉት ምንጮቹ ውጊያው አልተጀመረም እንጂ ዝግጅቱ አልቋል ሲሉ አስፈሪውን ሁኔታ ገልጸዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ከባድ ጭንቀትና ሽብር ውስጥ ነው ያለው የሚሉት ምንጮቹ ህወሃትም ሆነ የኦህዴዱ ስብስብ በጋራ ሊያካሂዱት ያሰቡትን የዘር ማጥፋት ወንጀል የማያቆሙ ከሆነ ነገሩ ሁሉ ከቁጥጥር ውጪ ሊወጣ ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በአንፆኪያ_ገምዛ ወረዳ የኦህዴዱ ኦነግ ሃይል ጦርነት መክፈቱን የኢትዮ 360 ምንጮች ገልጸዋል።
በተለይ በወረዳው ጫንጮ ፣ መስኖ፣ ሀገረማሪያምና ሟጨራን ጨምሮ በአካባቢው በይፋ በንጹሃን ላይ ጦርነት ከፍቷል ብለዋል።
ከህዝብ ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጠው ይሄ ሃይል ከባድ መሳሪያ ጭምር ወደ ህብረተሰቡ እያስወነጨፈ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በደብረሲና፣ ዶቃቂት እና ወፋ ዋሻ ላይ ይሄው የኦነጉ ሰራዊት በከባድ መሳሪያ በመታገዝ ንጹሃንን እየጨፈጨፈ ነው ብለዋል።
ይሄው ገዳይ ቡድን በወልደያ በኩል ላይ ሳንቃ ፣ወይንዬ ፣ጌሾ በር፣ ቃሊምና አካባቢው ላይ ጥቃት ለመክፈት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
ከወልደያ በቅርብ ርቀት አድፍጦ የሚገኘው ይሄው ገዳይ ቡድን ዋና ማረፊያውን ኩረታና ደንጐላ ላይ አድርጓል ብለዋል።
በቋራ በኩል ደግሞ ህብረተሰቡን ትጥቅ ፍቱ በሚል ከባድ ወከባ እየተፈጸመ አነው ይላሉ የኢትዮ 360 ምንጮች።
በተለይ በቋራ ገለጉ በኩል የመከላከያ፣የሚሊሻና የፌደራል ፖሊስ አባላት ነን የሚሉ ቤት ለቤት በመዞርና መሳሪያ ለመንጠቅ እየሞከሩ ነው ሲሉ የኢትዮ 360 ምንጮች ገልጸዋል።