(ኢትዮ 360-ሚያዚያ 3/2015)
የሶማሌ ክልል ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የክሉን ልዩ ፖሊስ መልሶ ለማደራጀት ተስማማቻለሁ ማለቱን ተከትሎ በሶማሌ ክልል ህዝባዊ ቁጣ መቀስቀሱን የኢትዮ 360 ምንጮች ገልጸዋል።
የኤረር ዞን የፊቅ ከተማ ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት የክልሉ ልዩ ፓሊስ መበተን የለበትም በሚል ቁጣቸውን ሲገልጹ መዋላቸውንም ይናገራሉ።
ዛሬ የፊቅ ከተማ ነዋሪዎች ብቻ አደባባይ ይወጡ እንጂ የትላንቱ የክልሉ ውሳኔ ግን መላውን የሶማሌ ህዝብን ማስደንገጡንና ማስቆጣቱንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
አስቀድሞ ልዩ ሃይሉን እንደማይፈታ በግልጽ የተናገረው ሙስጠፋ መሃመድ እንዴት ሃሳቡን ይቀይራል የሚለው ጉዳይም አጠያያቂ ሆኗል ይላሉ።
ዛሬ የኢትዮ 360 ምንጮች እንዳገኙት መረጃ ደግሞ ሙስጠፋ መሃመድ እኔ ልዩ ፖሊሱን እበትናለሁ ብዬ ቃል አልገብእሁም በሚል ከአብይ አህመድ ጋ አተካራ ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል።
ምናልባትም ሙስጠፋ ከትላንቱ ውሳኔ ጋር ተያይዞ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ለወንበሩ ስጋት ሳይሆን በፊት ነገሩን ለማብረድ የሚያደርገው ሙከራ ሳይሆን አልቀረም ሲሉም ይናገራሉ።
ፊቅ ላይ የተነሳው ተቃውሞ ወደሌሎች አካባቢዎች ከመዛመቱ በፊት ግን ሙስጠፋ መሃመድም ሆነ ሌላው አካል ሰልፈኞቹ ላነሱት ጥያቄ ምላሽ መስጠት አልቻሉም ሲሉ የኢትዮ 360 ምንጮች ተናግረዋል።