(ኢትዮ 360 - ታህሳስ 24/2012) በራያ አላማጣና አካባቢው እየተካሄደ ያለው አፈና እየተጠናከረ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 እንዳሉት አፈናው በዋናነት የሚካሄድባቸው አካባቢዎች በራያ አላማጣ በገጠርና በከተማ፣በራያ ኦፍላና ኮረም ከተማ፣ራያ አዘቦና ጨርጨር ከተማ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
አፈናው በጣም ተጠናክሮ እየተካሄደ ያለው ግን በማዕከላዊ ራያ አላማጣ አካባቢ መሆኑን ተናገረዋል።
እንዲህ አይነቱ አፈና በሰኔ 2010 ነው የተጀመረው የሚሉት ነዋሪዎቹ እስካሁንም ከ2ሺ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች መታፈናቸውን ይገልጻሉ።
ከታፈኑት ውስጥ በሕይወት መኖርና አለመኖራቸው የማይታወቀው በርካቶች ናቸው ይላሉ።
ባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ የአላማጣና የራያ አላማጣ ወረዳ የኢየሱስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መታገታቸውን ነው ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 የተናገሩት።
ከአፈናው ሌላ ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ራያ ነኝ በማለታችሁ ይቅርታ ጠይቁ ከሚለው ጀምሮ የሚደርስባቸውን የተለያየ አሰቃቂ ድርጊት ማቆሚያ የሚያበጅለት አልተገኘም ይላሉ።
የሕወሃት ካድሬዎች ባስተላለፉት ትዕዛዝ መሰረት ተማሪዎች በነፍስ ወከፍ አራት ኪሎ ስንዴ ይዘው እንዲመጡ ማድረግም ሌላው የህወሃት አስከፊ ድርጊት ነው ሲሉ በምሬት ይናገራሉ።
አየር ማረፊያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ደካማ አዛውንቶችን ይቅርታ ጠይቁ በሚል መሬት ለመሬት እየጎተቱ ከማሰቃየት ጀምሮ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን በአካባቢው እንዳይኖር ማድረግም የሰሞኑ የህውሃት ካድሬዎ ቅጣት ነው ብለዋል።
በየአዋሳኝ አካባቢዎችና በተለያዩ ቦታዎች በብዙ ሺ የሚቆጠር ሰራዊትን የማስፈር አካባቢውን ሰላም የመንሳት እንቅስቃሴም የህወሃት የተለመደ ድርጊት ሆኗል ሲሉ ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 ገልጸዋል።