የሲዳማ ክልል ፕሬዝዳንት የግል ጠባቂዎች በአካባቢው ፖሊሶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የኢትዮ 360 ምንጮች አስታወቁ።
የፕሬዝዳንቱ የአቶ ደስታ ሌዳሞ የግል ጠባቂዎች በሥራ ላይ ባሉት የፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት ያደረሱት ከትናንት በስቲያ በሀዋሳ ከተማ በታቦር ክፍለ ከተማ በ05 ቀበሌ መሆኑን ይናገራሉ።
የግል ጠባቂዎች ሲጠጡና ሲዝናኑ ካመሱ በኋላ የተገለገሉበትን ሒሳብ ሲጠየቁ አንከፍልም ማለታቸውን ይናገራሉ።
አንከፍልም ማለት ብቻ ሳይሆን የሆቴሉን ባለቤት ከደበደቡና የአንገት ሀብሉን በጥሰው ስወስዱም የሆቴሉ ባለቤት የይድረሱልኝ ጥሪ በወቅተ በመደበኛ ሥራ ላይ ለሚገኙ የፖሊስ አባላት ስልክ ደውሎ መንገሩን ገልጸዋል።
ፖሊሶቹ ወደ ሥፍራው እንደደረሱም እናንተ ወደዚህ ለምን መጣችሁ ከእኛ በላይ ማን አለና ነው የመጣችሁት በሚል በያዙት መሣሪያ ሰደፍ ከፍተኛ ጥቃት እንዳደረሱባቸውም ተናግረዋል።
ለፖሊሶቹ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ሁለቱ በአሁኑ ሰዓቶ ሀዋሳ ራፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።
ድርጊቱ በሀዋሳና አካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል ሲሉም የኢትዮ 360 ምንጮች ገልጸዋል።